Tuesday 9 July 2019

ከስልጠን ጀርባ የድብቅነት ስነልቡና አባዜ

ጌታቸው መላኩ (የሚዲያና ተግባቦት አማካሪ)
በ getachewmelaku@gmail.com ላይ ሊያገኙአቸው ይችላሉ፡፡

በትርክት ሰምተን ከፅሁፍ ሰነዶች አንብበን፣ ነገር ግን ልክ እንደኖርንበት ጊዜ የምናውቀው (ከጊዜው ቅርበት የተነሳ ይመስለኛል) የቀዳማዊ ሀይለስላሴ አገዛዝ በተለይ ከጣሊያን ሽንፈት በኋላ በአንፃራዊ ሁኔታ የተረጋጋ ነበር፡፡ ማሳያውም ለረጅም አመታት የዘለቀው የአገዛዙ ስልጣን ከሌለው አንፃር ረጅም መሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን ንጉሱ አለም ሲቀየር፣ ሀገር ወደ ውጪ እየተመለከተ ሲለወጥ ምልክቱን እንኳ መመልከት አቅቷቸው፣ እኛ በአለም ቢያንስ በግርማቸው የሚፈሩና የሚከበሩ ንጉስ እንደሰማነው በወታደሮች በትራስ ታፍነው ተገደሉ፡፡ ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ከስደት መልስ ሀገሪቱን ለማረጋጋት የሄዱበት መንገድ እጅግ አስተዋይ ያስባላቸው ነበር፡፡ ሀገሪቱ ከ1933 ዓ.ም በኋላ በአርበኛ፣ በስደተኛና በባንዳ ተከፋፍላ ለዘላቂ የስልጣን መደላድሉ አስጊ ጊዜ ላይ ነበረች፡፡ እንግሊዞቹ ሳይቀሩ ላራሳቸውም ይሁን ለሌላ ምክንያት ራስ አበበን የመሰሉ አርበኞችን ስልጣን እንዲዙ ቢያበረታቱም ይህንን ጊዜ ለማለፍ ንጉሱ ያለፉበት መንገድ አስገራሚ ቢሆንም ይህ ብልሀታቸው በተለይ አስተዋነታቸው በስተርጅና የት ገባ የሚሉም አሉ፡፡ ድብቅ አባዜ ይሆን ይሆን?
የደርግ ወታደራዊ ስብስብ አብዮቱን ጠልፎ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ የኢትዮጵያን የተማሪዎችና የሌሎች አብዮተኞችን ትግል መስመር አሳተው፡፡ በሁለት አዋጆች/ደንቦች መሬትን ላረሹ እንዲሁም "ትርፍ" የከተማ ቤትና መሬት ለመንግስት ብሎ አብዮተኛውን በእጅጉ ጥያቄና ምክንያት አሳጣው፡፡ ይባስ ብሎ ዴሞክራሲያዊ መብትን ለመደፍጠጥ መሞከሩ የፈጠረው በተለይ በህቡዕ ከሚንቀሳቀሱ አካላት ጋር የፈጠረው መላተም ብዙዎች ህይወታቸውን የገበሩበትን ክፉ አጋጣሚ ፈጠረ፡፡ አሁንም በደርግ ወታደራዊ ቡድንም ይሁን በህቡዕ በሚንቀሳቀሱት አካላት ውስጥ የራሳቸውም ሆነ ኢትዮጵያዊ የሆነ የድብቅነት ስነልቡና ተጠቂዎች ያደረጋቸው ስሪት እንዳለ ይሰማኛል፡፡ በተጨማሪም የአሸናፊና ተሸናፊው ስልቡና አሁንም ድረስ እያማሰነን ይገኛል፡፡
ኢህአዴግና ሻቢያ ለአመታት የዘለቀ "ከቀኝ ገዢ" ስርአት የመላቀቅና  የራስን ክልል "ነፃ የማውጣት" ጦርነት እንዲሁ በድብቅነት ስነልቡና በተጠናወተው ምክንያት ተሸፍነው ባደረጉት ተጋድሎ አንዷ ሀገር ሁለት ሆነች፡፡ ለዘመናት በድብቅ አጀንዳ ተታሎ ነፃ የመውጣት እንቅስቃሴውን የደገፈው ህብረተሰብም የሌላ ዙር "ቀኝ ገዢ" ሰለባ  ሆኗል ብለው የሚከራከሩ ብዙሀን ናቸው፡፡ የማይታበለው ሀቅ ግን ብዙዎች የስኳር ነገር አልሆን በሏቸው የድብቅ ነፃ አውጪነት ካባቸው እስኪገለጥ ድረስ ሞሰኑ፣ ነቀዙ፣ ተበላሹ ድመት ብትመነኩስም አስተረተባቸው፡፡ ይህም የድብቅ ስነልቡናቸው መገለጫ ሆኖ ወጣ፡፡ ከኢህአዴግ ውስጥ ጊዜው እድል የፈጠረላቸው ከወስጥ ገፍተው ስልጣን ሲይዙ ከውጪ የነበረውን ግፊት በመመልከት የጠለፋ ያህል የጥያቄው ወራሽ ሆነው ብቅ ያሉት እነዚህ አካላት የድብቅ ስነልቦናው ችግር ተጠቂ ይሁኑ አይሁኑ ጊዜ የሚፈታው ጉደይ ነው፡፡
የሚገርመው ነገር ይህ የድብቅነት ስነልቡና ችግር በመንግስትነት ባሕርይ ሁሉንም ሲጎዳ ጎልቶ ይታይ እንጂ አጋጣሚዎች እያሳየን ያሉት ይህ የድብቅነት ስነልቡና በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በድርጅትና በማህበረሰብ ደረጃ የሚንፀባረቅ ችግር መሆኑን ነው፡፡ ከጓደኝነት ጀርባ ሌላ ድብቅ ስነልቡና፣ ከትዳርና ቤተሰብ ምስረት ጀርባ ሌላ ድብቅ ስነልቡና፣ ከድርጅት ባልደረብነት ጀርባ ሌላ ድብቅ ስነልቡና፣ ከማህበረሰብ አባልነት እንዲሁም ወኪልነት ጀርባ ሌላ ድብቅ ስነልቡና፡፡ ከአነቃቂ ንግግር አቅራቢነት ጀርባ ሌላ ድብቅ ስነ ልቡና፣ ከስራ ፈጠራ ስኬት ጀርባ ሌላ ድብቅ ስነልቡና፣ ከበጎ አድራጎት ተግባር ጀርባ ሌላ ድብቅ ስነልቡና፣ ከፓርቲ አባልነት ጀርባ ሌላ ድብቅ ስነልቡና፡፡ የድብቅ ስነልቡናው ዝርዝር በየፈርጁ ማለቂያ ሳይኖረው ሊቀጥል ይችላል፡፡ ከተቃዋሚነት ጀርባ ሌላ ድብቅ ስነልቡና፣ ከደጋፊነት ጀርባ ሌላ ድብቅ ስነልቡና፣ ከፓርቲ መሪነት ጀርባ ሌላ ድብቅ ስነልቡና፣ ከሀገር መሪነት ጀርባ ሌላ ድብቅ ስነልቡና ዝርዝር ያደክማል፡፡
ለዚህ ጉዳዬ አስረጅ እንዲሆነኝ እስቲ እንድ ምሳሌ ላንሳ፡፡ የሰሞኑ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ጉዳይ እጅግ የሚገርም ነው፡፡ በየማህበራዊ ሚዲው የሚገልፀውና የሚሰራጨው መልእክት፣ ኢሳት ባለደረቦቹን በአመለካከታቸው ምክንያት የማግለል ስራ እየሰራ እንደሆነ ሲሆን፤ ድርጅቱ ያወጣው ግልፅነት የጎደለው መግለጫ (ለአላማ እንደሆነ በድንብ ስለሚያስታውቅ ኢሳቶች ቢያስቡበት መልካም ነው) ደግሞ የሚያትተው የለውጥ ሂደት እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሆነ ነው፡፡
ኢሳት በሀገሪቱ ለመጣው ለውጥ እንደ ብዙሀን መገናኛ ጣቢያ ዋነኛ ድርሻ እንዳለው የማይታበል ነው፡፡ ብዙዎች ግን ሙያዊ ስነምግባርን በተለመከተ በኢሳት ላይ ጥያቄ አላቸው፡፡ በጊዜው ኢሳት የነፃ አውጪ አይነት እንቅስቃሴ በስሜት ያደርግ ስለነበር ይመስለኛል፡፡  የዚህ አይነቱ የብዙሀን መገናኛ ስነምግባር የማይደገፈው በምክያትና በማስረጃ ከሚያምን ተከታይ ይልቅ ስሜቱን የሚከተል ተከታታይ መፍጠሩ ነው፡፡ የሚገርመው ይህ ተከታታይ ሁኔታዎች የተቀየሩ ዕለት በራሱ በጣቢያው ላይ መነሳቱ የማይቀር ነበር፣ እንሆ ሆነ፡፡
የለውጡን መምጣት ተከትሎ በኢሳት ውስጥ በተለይ በተፅእኖ ፈጣሪነታቸው የሚታወቁት ግለሰቦች የለውጡ ግልፅ ደጋፊ ሆነው መምጣታቸው ባያስገርምም፣ በኢሳት ውስጥ ለሀሳብ ልዩነት የሚሰጠው ቦታና ግምት እንደተወራውና እንደተዘመረው እንዳልነበር የሚያሳዩ ነገሮች ከለውጡ መምጣት ማግስት ጀምሮ መከሰት ጀምረው ነበር፡፡ ይህም አብዛኛውን ተመልካችና አድማጭ አሁን ከአንድ ዋንጫ መጠጣት ሊቀር ነው፤ የሀሳብ ፍትጊያ የሚያመጣውን ልዕልና ልናይ ነው፤ ያለው አድማጭ ተመልካች በርካታ ነበር፡፡ በእርግጥ በኢሳት ላይ የነበረውን የቆየ የብዙሀን መገናኛ ጣቢያነት ሚናን ያኮሰሱና የነፃ አውጪ ግንባርነት ሚናን ያላበሱ የቀን ተቀን አሰራሮች በብዙዎች ዘንድ አልተዘነጉም፡፡ እንዲሻሻሉ ለማገዝ ያሰበና መሳተፍ የቆረጠ ሰው ቢያንስ በእኔ ዙሪያ እንደነበር አውቃለሁ፡፡  
ነገር ግን አሁን ሁኔታዎች የሚያሳዩት እንደ ሌላው ሁሉ ኢሳትም የድብቅ ስነልቡና ችግር ተጠቂ የሆነ ጣቢያ መሆኑን ነው፡፡ በእርግጥ ከአሀገራቸው ተሰደው የነበሩ ግለሰቦች ወደ አገራቸው የመመለስ እድል ማግኘታቸው አስደሳች ነው፣ ለእነሱም፣ ለቤተሰባቸውም እንዲሁም ለወዳጅ ዘመዳቸው፡፡  ከጥቂት ቀናት በፊት ታማኝ በየነን አንድ ሆቴል ውስጥ በአካል ስመለከተው እኔንም ለየት ያለ ስሜት እንደተሰማኝ ልደብቅ አልፈልግም ፡፡ ከሀገር ከወገን በተለይ የመለየት ሰሜቱ ለኢትዮጵያዊ ካልደረሰብት በቀር ለመረዳት ስለሚከብድ ባልፈርድም  ለማስረዳት ግን ከባድ ጉዳይ የሚሆንብኝ ይመስለኛል፡፡ ለጥቂጥ አመታት ለትምሀርት እንኳ ሀገርን ሲለዩ የሚሰማው ስሜት ባያስቸግረኝም ጎሻሽሞኛል፡፡ ነገር ግን የኢሳት ባልደረቦች በተለይ "ተፅዕኖ ፈጣሪ" ሰዎች ድብቅ አላማ ወደ ሀገር ቤት የመግቢያ እድል ለማግኝት ወይስ እውነተኛ የሰላምና የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት የሚደረግ ጥረት ድጋፍ፡፡
የድብቅ ስነልቡና መነሻው ምንም ይሁን ምን ችግሩ ግን ግለፅ ነው፡፡ በመጀመሪያ ግለሰቦች ባለባቸው የድብቅነት ስነልቡና ምክንያት የረጋና የተመቻቸ ህይወት እንዲሁም ውጤታማነት ሲርቃቸው፤ በአንድ አጋጣሚ የሰሩትን መልካም ስራ በሌላ ጊዜ በተቃራኒው እያጠፉ የመኖር አባዜ ውስጥ ይከታቸዋል፡፡ ድርጅቶችም እንደዚሁ ብዙ ድብቅ ስነልቡና ባላቸው ግለሰቦች ተወጥረው የአመፃና የተንኮል አውድማ ሲሆኑ፣ የማደግና የመለወጥ እድላቸው መክኖ ለሌሎች ውድቅና ክሽፈት ምክንያትም ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ ድብቅ ስነልቡና በሀገር ደረጃ ያስከፈለንን ዋጋ ስንመለከተው ከበሽታነቱ አልፎ ሞተን ወደ መቃብር ካልወረድን የማይተወን ክፉ ደዌ እንደሆነብን የተረዳን አይመስለኝም፡፡
በተለይ የወላጅ፣ የአስተዳዳሪ፣ የአመራርና የእናትነት/የአባትነት ሃላፊነት ያለባቸው ሰዎች የድብቅነት ስነልቡናው ችግር ተጠቂነት እየጨመረ መምጣቱ ወላጅ አልባ፣ አስተዳደሪ የማይበረክትለት፣ መሪ ያጣ፣ እጓለማውታን አድርጎን እነሆ ለዘመናት ዘለቀ፡፡ ለመፍትሄው ማን ምን ያስብ ሆን? የድብቅነት ስነልቡና በእኛ ሀገር በሰፊው መገለጫ የሆነው "የጠላቴ ጠላት ለእኔ ወዳጄ ነው" በመሆኑም፤ ጠላቱ የጠፋ ዕለት ወዳጅነትን የሚያዘልቅ አላማም ይሁን ተነሳሽነት ሲጠፋ ይስተዋላል፡፡ "እውቀት የጎደለው ይጎዳል አስተወሎት የጎደለው ደግሞ እጅግ ይጎዳል" ነውና በጠላቴ ጠላት አላማ መስተጋብር የፈጠረ ሁሉ ጠላቱ ሲጠፋ ወይም ሲዳከም አስተውሎ የጎደለው ስለሆነ ከጠላቱ በላይ መበታተኑ መድከሙና መውደቁ ያስገርማል፡፡ ድብው ስነልቡናና አባዜው ማለት ይህ ነው፡፡
ከሙያና ከመስሪያ ቤት ምርጫ ጀርባ ድብቅ ስነልቡና፣ የፖለቲካ ፓርቲ ከማደረጃት ጀርባ ድብቅ ስነልቡና፣ የብዙሀን መገናኛ ድርጅት ከማደራጀት ጀርባ ድብቅ ስነልቡና፣ የበጎ ድራጎት ድርጅት ከማቋቋም ጀርባ ድብቅ ስነልቡና፣ ከሰፈር ልማት አስተባበሪነት ጀርባ ድብቅ ስነልቡና እንዲሁም ሲብስ ጓደኝነት ከመመስረት ጀርባ ድብቅ ስነልቡና ወዘተ... ኢትዮጵያዊነታችንን አውርደውታል፡፡
መድረሻችን የት ይሆን?
ድብቅ ስልቡና የግልፅ ስነልቡና ተቃራኒ ነው፡፡ በግልፅ ንልቡና ሰዎች የምንሻውን እንመኛለን፡፡ እርሱን ለማግኘት እንጥራለን፡፡ ሌሎች ፍለጎታችንንና ጥረታችንን ተመልክተው ሊረዱን ባይችሉ እንኳ ምንገዳችን ላይ በመቆም ደንቃራ ከመሆን ይታቀባሉ፡፡ በዚህ የቀጠለና ያደገ የግልፅነት ስነልቡና ግንዛቤ ባይኖ መማርን፣ ቢሳሳቱ ማረምን፣ ቢበድሉ ይቅርታ መጠየቅን ስለሚያስተምርና በውስጣችን ስለሚያዳብር መለወጥ እንችላለን፡፡ በመሆኑም ግለሰባዊ እድላችን፣ እንደሀገር ፅዋ ተርታችን በተጠናወተን የድብቅ የስነልቡነ ችግር  እንዲቀረፍ ብንተጋ፡፡ ግላዊ አስተሳሰብና አመለካከት ክቡር ሆኖ ሳለ ለድብቅ ስነልቡና የሚዳርገን ችግር በትውልድ ላይ ብንሰራ፡፡ 

No comments:

Post a Comment