የሀገራችንን
ፖለቲካ በእንክሮ የሚከታተለው ሰው ብዛቱንና፤ ፖለቲካው ገብቶት ነገሮችን መተንተን የቻለው ህዝብ ዝምድናው ለየቅል መሆኑ እሙን
ነው፡፡ ነገር ግን ፖለቲካው አፍጦ የመኖርህ ጉዳይ ላይ ጥያቄ ቢያስነሳ ማንም ሰው ምንም ሊሆን እንደሚችል ግልፅ ነው፡፡ ይህ ነገር በእርግጥ በሀገራቸው ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ላይ ከሚሳተፉት ሰዎች መካከል
ምን ያህሉ በግንዛቤው አላቸው ብሎ መገመት ቢከብድም መልሱ ሊሆን
የሚችለው እንደ ሀገሩ ጠባይ ይመስለኛል፡፡
የፖፕ
ሙዚቃ ንጉሱ ማይክል ጃክሰን በገነነበት በአስራ ዘጠኝ ሰማንያዎቹ አንድ የቴክሳስ ገበሬ የአሜሪካን ፕሬዚደንት ማን እንደሆነ ተጠይቆ
ሲመልስ ማይክል ጃክሰን ማለቱን ብዙዎች የተረኩትና በግርምት አንዳንዶች ደግሞ በፈገግታ የሚያስታውሱት ጉዳይ ነው፡፡ ልብ በሉ ወዳጆች
ይህ የቴክሳስ ገበሬ የጠፉበት ፕሬዚደንት በመላው አለም እጅግ ዝነኛ የነበሩት ሮናልድ ሬገን ነበሩ፡፡ ገበሬው የሮናልድ ሬገን ይሁን
የማይክል ጃክሰን ጉዳይ ለእሱ ምኑም አይደል፡፡ ለእሱ ወሳኙ ጉዳይ እርሻው አዝመራው፣ ሲገፋም የምርት ውጤቶች የገበያ ዋጋ ነው፡፡
ይህ ገበሬ ለምን እንዲህ አላሳብክም? ለምን እንዲህ አልተረዳህም? የሚለውና የሚጎተጉተው ካድሬ የለም፡፡ እሱም ይህንን የሚያስብበት
ጊዜ የለውም፡፡
ከዚህ
ጋር በተነፃፃሪ “የጡቄ ገበሬ ማህበር ነዋሪዎች የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በሰላማዊ ሰልፍ መቃወማቸውን” በዜና ያሰማንን የደርግ
የካድሬዎች የስራ ውጤት አሁንም እየተዝናናንበት እንገኛለን፡፡ ከሁሉም በባሰ ነፍስ አውቀን በደረስንበት ዘመን የኢህአዴግ ተረት
ተረትና ውጤት ተኮር፣ ውሃ ማቆር፣ ሰው ማደንቆር የመሳሰሉት ትርክቶች የካድሬው የስራ ውጤቶች ሲሆኑ፡፡ እነዚህ ደግሞ ካድሬው የህልውና
ዋስትናዎች ነበሩ፡፡ ታዲያ የዛሬው ኑዛዜዬ ይህንን የተመለከተ ነው፡፡ እነዚህን ካደሬዎች ኢህአዴግ ሲያስፈለፍለበት የነበረውን የኢትዮጵያ
ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ (አሁን ዩኒቨርሲቲ ሆኗል)
ይህንን
ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ስቀላቀል ሁለት ዋነኛ ምክንያቶች ነበሩኝ፡፡ አንደኛው የግል ጉዳይ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሙያ ጉዳይ
ነው፡፡ በእርግጥም በግል ዝንባሌዬና የትምህርት ዝግጅቴ በትምህርትና የትምህርት አስተደደር ስለነበር በዘርፉ ማስተማር፣ መመራመር
እንዲሁም ሙያዊ የአስተዳደር ስራ (የትምህርት አስተዳደር ማለቴ ነው)
መስራት ነበር፡፡ በዚህም የስራ፣ የማደግና በትምህርት ዝግጅት የመጨመር እድሌን እንደግለሰብ አስልቼ የገባሁበት ስራ ነበር፡፡ ሁለተኛው
ሙያዊ ምክንያቴ ያልኩት ሀገራችን ውስጥ ያለው የሲቪል ሰርቪሱ አገልግሎት እጅግ ደካማ፣ ሙስና ስሩን የሰደደበት፣ ስንፍናና ብክነት
የበዛበት ከዚያም በሻገር ለሀገሪቱ መቆርቆዝ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ዘርፍ ስለነበር ይህ ከአንድ ሚሊዮን በላይ በፌደራልና
በክልል አደረጃጀቶች ውስጥ የሰው ሀይል የያዘ ሴክተር እንዲለውጥ ዘላቂ፣ እስትራቴጂያዊና ወሳኝ ስራ መሰራት አለበት፡፡ ይህንን
ጥረት በመደገፍ የበኩሌት አስተዋፅኦ ለማድረግ መቀላቀሌን ስናገር በጊዜው የገጠመኝን አንድ ነገር በማስታወስ ነው፡፡
ለቅጥር
በሚደረገው የቃለመጠይቅ ምዘና ከአርባ በላይ ባለሙያዎች ተጠርተው ነበር፡፡ በዚህ ምዘና ውስጥ ካለፉትና ከተቀጠሩት ሶስት ባለሙያዎች
መካከል አንዱ ነበርኩ፡፡ በዚህ አጋጣሚ በጊዜው ተወዳድረው ከተቀጠሩት ባለሙያዎች መካከል በሀገር ደረጃ የሚታወቁ ግለሰቦች አሉ፡፡
ወደ ጉዳዬ ልመለስና በጊዜው የቃለ መጠይቅ ምዘናዬን አድርጌ ስወጣ ከመልማዬቹ መካከል አንዱ የኮሌጁ ነባር ሰራተኛ ተከትሎች ልጅነት
ቁመናዬን በመመልከት “አንቺ ጎረምሳ ይሄ ቤት ይሆነኛል ብለሽ ነው” ብሎ በወዳጅነት መንፈስ የጠየቀኝንና እኔም ነገሩን በመረዳት
የመለስኩት ትዝ ይለኛል “አይ ጋሼ ልሞክረው ብዬ ነው” የሚለው መልሴን እስከ ሁኔታውና ቦታው ጭምር አሁን የሆነ ያህል አስታውሰዋለሁ፡፡
ቅጥራችን
ተከናውኖ እኔም የእንድ ኮሌጁ ካደራጃቸው ሶስት ተቋማት ውስጥ የአንደኛው የትምህርት ጉዳይ ስራ አስኪያጅ በመሆን ስራዬን ጀመርኩ፡፡
በነበረኝም የስራ ሀላፊነትና በርካት አዳዲስ ነገሮችን ለማተዋወቅ የሞከርኩ ሲሆን ለዚህ መጣጥፍ እጅግ የጠቀመኝን ጉዳይ ውሎ አድሮም
ጉዳዮችን በጥልቀት ስገነዘብ ልቤን አሸፍቶ ከድርጅቱ እንድለቅ ያስገደደኝ ምክንያት ተከሰተ፡፡
አንድ
ልዩ ነገር ለመስራት ያሰብኩት የየክፍሉን የቀድሞ ተማሪዎች ማህበር በማቋቋም ለየትምህርት ክፍሎቻቸው እንዲሁም በአጠቃላይ ለኮሌጁ
አስተዋፅኦ የሚያደርጉበት መንገድ ለመቀየስ ነበር፡፡ ይህን ሀሳብ የወለደው ዋነኛው ገጠመኝ በጊዜው ለድህረ ምረቃ ተማሪዎች ብቁ
መምህራን ማግኘት እጅግ አስቸጋሪና ፈታኝ ጉዳይ ስለነበር ለዚህ እንዲረዳን በማሰብ ሲሆን፤ ለዚህም በጊዜው ከየትምህርት ክፍሎቹ
ተመርቀው በመውጣት በከፍተኛ የመንግስት ሀላፊነት ላይ ያሉ ግለሰቦችን በማወቃችን ነበር፡፡
ይህ
ጥረት አሳ መጎረርጎር ሆነና ያልታሰብ ነገር ጎትተን እንድናወጣ አስገደደን፡፡ በሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት ስልጣን ላይ ነበሩት
ግለሰቦችን ስምና የአካዳሚ ውጤት ስንመለከት በዚህ ደረጃ ውጤት አግኝቶ የተመረቀ ተማሪ እንዴት ተራ ነገር መረዳትና መግለፅ ይከብደዋል
ብዬ ራሴን መጠየቅ ጀመርኩ፡፡
ትንታኔዎች
እንደሚሉት ትምህርት የግብአት፣ የሂደትና የውጤት ትርጉም እንደመሆኑ መጠን በዚህ ሂደት በአንዱ ቦታ ላይ የሚፈጠር እንከን መላ
ውጤቱን እንደሚያባክነው ይታወቃል፡፡ የምርት ብክነት በኪሳራ ይመዘገባል፡፡ ለማሻሻልም የአመራርና የአሰራር ለውጥ በማድረግ ሊሻሻል
ይችላል፡፡ ይህም በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ሊፈፀም ይችላል፡፡ የሰው ልጅ በትምህርት ምክንያት መባከን ግን የትውልድ (በታወቀው መለኪያ
30 አመት) ጉዳይ ሲሆን ከዚያም እየተሻገረ የባከነው ትውልድ ሌላ የባከነ ትውልድ እየፈጠረ ለዘመናት የሚሻገር ችግር ይተውልናል፡፡
ይህንን ችግር ነው እንግዲህ በኢህአዴግ ላይ የተመለከትኩት፡፡
ከኢትዮጵያ
ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ የተመረቀው በሙሉ ችግር አለበት ባልልም በርካታው ግን በዚህ ችግር የተጠቃ ይመስለኛል፡፡ በመሆኑም ይህ በትምህርት
ብክነት የተጎዳ ማህበረሰብ አንድ ኢህአዴግ የተባለ ሀገር የሚመራ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ በብዛት ተሰግስጎ የሚገኝና ከባድ ችግር
የሚታይበት አካል ሆነ፡፡ ከሙያዊ ስነምግባር እስከ ሀገራዊ ሀላፊነት ድረስ የሚታሰቡትን ችግሮችን ለመፍታት የትምህርትም ይሁን የስነልቡና
ዝግጅት የሚጎድለው የሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ምሩቅ ፓርቲውን እንደ ተገን በመጠቀም ሲቪል ሰርቪሱ ይበልጥ በሙስና በአድሎአዊ አሰራር
(በጎሳና በብሄር ወገንተኝነት) በመፍጠር በየጊዜው በውድም በግድም ሲተገበሩ የነበሩት የለውጥ መሳሪያዎችን አፈር ያበላ ማህበረሰብ
መፍጠር የቻለ ተቋም ነው፡፡ እዚህ ላይ አንባቢ ቢፒአር (BPR) እና ቢኤስሲ (BSC) የተባሉትን ስትራቴጂያዊ የስራ አመራር መሳሪያዎች
ታሪካዊ አመጣጥና አተገባበር እንዲሁም ያመጡትን ውጤት ቢመለከት ለመፍረድ የረዳዋል እላለሁ፡፡
እናም
በሲቪል ሰርቪስ ምሩቃን የተሞላው ኢህአዴግ ግለሰቦቹን በሀገር ፍቅርና በህዝብ ወገንተኝነት ያልገነባ በመሆኑና በርካቶች እጅግ ሲበዛ
ሌብነትን እንደ ሙያ የተማሩ፣ አላዋቂነትን እንደጌጥ የሚያንጠለጥሉ፣ ሁለት መስመር አንብቦ ከመመርመር ይልቅ በስማ በለው የተነገረን
ነገር እንደ እውነትና ፍፁም መስመር የሚቀበል አባል ባለበት፣ በሀገራችን ያለው ስር የሰደደ ችግር ገፍቶት አባል በመሆን መጠጊያ፣
ሲያልፍም መኩሪያና ሀብት ማካበቻ እድል የሰጠውን፣ ሳይገባውና ሳይገባው በተለያየ የትምህርት እድል ከፍተኛ ጥቅም ያገኘ አባል የበዛበት
ኢህአዴግ በመጨረሻ ራሱን የሚበላበት ጊዜ እነሆ ደረሰ፡፡
አኔን
የሚገርመኝ አንደዚህ አይነት አደረጃጀት ውስጥ ያለው ኢህአዴግ ለ28 አመታት ኢትዮጵያን የሚመራ ፓርቲ የሆነበት መንገድ ነው፡፡
በእርግጥ ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡ ለበርካታ አመታት የዘለቀው ድህነት፣ በፖለቲካ አስተሳሰብ ምክንያት በጠራራ ፀሀይ የሚወደው የተገደለበት
ህዝብ ሞትን ፈርቶ ዝም ቢልም ይህንን ያህል ዝም ማለቱ ምን ያህል በድብርት ስሜት ውስጥ እንዳለ የሚያመላክት ነው፡፡ ለማንኛውም
ኢህአዴግ ፈረሰ፡፡ ኢህአዴግ በሀገረችን የፈጠረው የደካማ፣ ያላዋቂና የሌባ ስርአት ይፈርስ ይሆን?
አንባቢ
ልብ እንዲል የምፈልገው እኔ የውጤታማ ስራ አመራር ባለሙያ እንጂ የመጣ የሄደውን መንግስት ደጋፊ ወይም ተቃዋሚ አይደለሁም፡፡ በስራ
ውስጥ ድክመት ፈተና እንዲሁም ወደኋላ መመለስ ሊኖር ይችላል፡፡ ከአንባቢም እንደሚርዳው መንግስታት የሚመጡት ከአንዳች እንከን ጋር
ስለሚሆን ሁለጊዜ የምመለከታቸው በምክንያታዊ ትችትና ምስጋና ነው፡፡ እኔ ትንቢት ጠባቂም አይደለውም፡፡ ምልክት የሚሻም ሰው አይደለሁም
ክፉ ትውልድ ምልክት ይሻልና፡፡ እኔ የምፈልገው አሁን በፊት ለፊቴ ያለውን እውነታ በምክንያታዊነት መተንትንና መረዳት ላይ ነው፡፡
ለሌሎች ምክር የሚሆንው ግን የኢህአዴግ መፍረስ ስመኝ የነበረው ሌላ የመላእክት ፓርቲ ይመጣል ብዬ ሳይሆን፣ አንዴ እድል አግኝቼ
ከዚህ በኋላ ነገሮች ስር ሳይሰዱ የምታገልበት ሁኔታዎች እንዲመቻችልኝ ነበር፡፡
እድለኛ
ነኝ!!!!!
No comments:
Post a Comment