የኮሮና
ወግ
(የማይሸጥ
ትዝብታዊ ትንተና)
ክፍል አንድ
ጌታቸው መ ይትባረክ
ሰሞኑን በየቀኑ ከሚሰሙኝ ጥያቄዎች መካካል የኮሮና ጉዳይ ዋናው
ሊሆን እንደሚችል ብዙዎች ሊገምቱት የሚችሉት ይመስለኛል፡፡ ከስራ ባልደረቦች ጋር በእኛ ህይወት ዘመን ይህ መከሰቱ የሚሰጠንን ትርጉም
እንስተን ምሳ እየተቋደስን ስንጨዋወት ባለደረባዬ “ሁሉም ጊዜው፣ መጠኑና አይነቱ ይለያይ እንጂ እንደዚሀ አይነት ጉዳይ ይገጥመዋል”
ብሎ ስሜቴ የማንኛውም ሰው አይነት ስሜት ሊሆን እንደሚችል ገምቷል፡፡ ለጊዜው ብቀበለውም የኮሮና ጉዳይ ግን ወደ ሀገራችን መግባቱን
ተከትሎ (ይገርማል! “መግባቱን” የምንለው ለወትሮው ከውጪ የሚገባ ዕቃን ነበር) ከስራዬም ከቀን ተቀን ውሎዬም ጋር ተገናኝቷል፡፡
የኮሮና
ገጠመኝን አንዳንዶች ሀይማኖተኞች እምነት የሚፈተንበት አንዱ ክስተት እንደሆነ ሲገልፁት፣ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ደግሞ ክስተቱ
የሚፈጥራቸው ምጣኔ ሀብታዊ ውልደቶች ቀልባቸውን ይስበዋል፡፡ ከህክምና ባለሙያዎችን ጋር በጥልቀት ባልወያይም ዘመናቸውን የፈተነ
አንድ የጤና ጉዳይ እንደሆነ ግን የሚያስተባብሉት ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በኋላ ያልተመለስንበት በጊዜው
አሪፍ የነበርንበት የባዮሎጂ ትምህርት እውቀታችንን ስናስታውስ (አዲስ እውቀት ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ካልተጨመረ በስተቀር
ማለቴ ነው) “ቫይረስ ህይወት በሌለው ነገር ውስጥ መቆየት እንደማይችል” የሚል እናገኛለን፡፡ ነገር ግን የኮሮና አማጪ ቫይረስ
(COVID 19) ብረት ነክ፣ ልብስ ነክ፣ ፕላስቲክ ለክና ሌሎችም ነገሮች ላይ ከሰአታት አልፎ ለቀናት እንደሚቆይ ስንረዳ በእርግጥም
የዘርፉ እውቀት ዘመናትን ተሻግሮ እንዳለፈ ተገነዘብኩ፡፡ የኮሮና ቫይረስ ላዩ በፕሮቲን ንጥረ ነገር የተሸፈነ በመሆኑ እንደሌሎች
ቫይረስ አይነቶች ህይወት ካለው ነገር ወጥቶ ለሰአታት ሲገፋም ለቀናት መቆየቱ ልዩ ስለሚያደርገው እጅን ልክ ስጋ ወጥ በልተን (አንዳንዴ
ሽታው ባይቀርልንም) ቢያንስ ቅባቱን ከእጃችን ለማስወገድ በሙቅ ውሀና በሳሙና በደንብ የምንታጠበው ነገር ትዝ እንዲለኝ አድጓል
(በፆሙ)፡፡
ከእነዚህ
በላይ ግን የሴራ ተንታኞችን ያህል ጉዳዩን ሳቢ ያደረገው ሰው አልታየኝም፡፡ አንዳንዶች ሀይማኖት ነክ ሴራ በቀጠታ በአለም “እምነት”
ባላቸው ህዝቦች ላይ የተቃጣ ጉዳይ አድርገው ሲያቀርቡት ሌሎች ደግሞ በሰብአዊ ፍጥረት ላይ በሆኑ አካላት የተነጣጠረ ጉዳይ አድርገው
ማስረጃ እየጠቀሱ ታሪክ እየበረበሩ በብዙሀን መገናኛና በማህበራዊ ብዙሀን መገናኛ ሳይቀር ሀሳባቸውን ያቀርባሉ፡፡ ከነዚህ ባልተናነሰ
ሁኔታ ጉዳዩ ምንም አዲስ ነገር እንዳልሆነና ውሀ የማይቋጥርን ጉዳይ ወሬውን በማራገብ ብቻ ትልቅ አለማቀፋዊ “አጀንዳ” እንዲሆን
መደረጉን የሚከራከሩ አካላት ደግሞ ብቅ እያሉ እንደሆነ ሰሞኑን በምከታተላቸው የግለሰቦች ውይይትና ክርክር እንዲሁም የማህበራዊ
ብዙሀን መገናነኛ ውጤቶች ልመለከት ችያለሁ፡፡
እውን
ግን ኮሮና ምንድን ነው? የጤና ችግር፣ የምጣኔ ሀብት ችግር፣ የእምነት ፈተና፣ የመጨረሻው ዘመን ምልክት፣ በጥቂት የሰው ዘሮች
ላይ የተቃጣ ሴራ ወይስ በአጠቃላይ የሰው ዘር ላይ የመጣ መከራ አሊያስ ዝም ብሎ የተፈጠረ “የዶቅማ” ወሬ፡፡
እኔን
ጨምሮ በርካታ ግለሰቦች ወዳጆችን ጨምሮ ከበሽታው ይልቅ በሚሰማ ማንኛውም ልዩና ያልተለመደ ስሜት መሸበር ከጀመርን ቀናት እየተቆጠሩ
ነው፡፡ ሙቀቴ ጨመረ፣ ሆዴ ተረበሸ፣ ሳል ነገር ሞከረኝ፣ ምግብ ፍሎጎተ ቀነሰ፣ ራስ ምታት ተሰማኝ ወዘተ… ከዚያስ? ከዚያማ፣ ኮሮና
ይሆን እንዴ ነዋ!! ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ሳይሆን አልቀረ፡፡
No comments:
Post a Comment