Tuesday, 9 July 2019

አሮጌ ሀሳብን አዲስ ልብስ ማልበስ እንዳይሆን


አሮጌ ሀሳብን አዲስ ልብስ ማልበስ እንዳይሆን
ጌታቸው መላኩ (የሚዲና ተግባቦት አማካሪ)                        

ሰሞኑን አንድ ለውጥ ተኮር በተለይ ድርጅታዊ ለውጥ ተኮር ጉዳይ ላይ ሀሳቤን እንዳካፍ በአንድ ድርጅት ከፍተኛ አመራር ተጋብዤ ነበር፡፡ ግብዣው ሳይገርመኝ አይቀርም፡፡ ምን ትልቅ ነገር ሰርቼ ነው የእኔን ሀሳብ ለመጋራት የተጋበዝኩት የሚል ሀሳብም ውስጤ ይብላላ ጀመር፡፡ ወደ አእምሮዬ ጓዳ በመዝለቅ የተለየ ነገር ፍለጋ ስባክንም ሰነበትኩ፡፡ ወደ መረጃዎቼና መፃህፍቶቼም ማስቀመጫ አልፌ ልዩ ነገር ፍለጋ ቀናትን አጥፈቼ ነበር፡፡ ያላስቀመጡትን ፍለጋ ማለት ይህ ነው!!!
ለማንኛውም ጠሪ አክባሪ ነውና ያለችኝን ለማካፈል ወስኜ ለማዘጋጀት ሳስብ ሁለት አጋጣሚዎች እንደ መልካም አጋጣሚ ተከሰቱልኝ፡፡ አንደኛው የማህበራዊ ብዙሃን መገናኛ ላይ ያየሁት በድርጅቶች አመራር መካከል የትውልድ ልዩነት ሲኖር መስተጋብሩ ምን ይመስላል? ልዩነቱ አሳሳቢስ ከሆነ ምን ማድረግ ይበጃል? የሚል ጉዳይ ነበር፡፡ በዚህም የተለያዩ ታዋቂ የድርጅት ዘላቂ አመራር ባለሙያዎች ያወሱትን ጉዳይ ሳሰላስል ቆየሁ፡፡ በዚያ ላይም ተመርኩዤ ሀሳቤን በማደራጀት ላይ እንዳለሁ ሁለተኛው ገጠመኝ ተከሰተ፡፡
ሁለተኛው ገጠመኝ በኢትዮጵያችን ያሉ በተለይም በዋናነት ከውጪ ሀገር በስደት ቆይተው የዶ/ር አብይ ቡድን ወደ ስልጣን መምጣቱን ተከትሎ በተፈጠረው ምቹ አጋጣሚ የገቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች መክሰማቸውን ሰማሁ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ አዲስ ፓርቲ ለማቋቋም ስብሰባዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ተመለከትኩ እንዳዶቹንም ለመታደም ሞከርኩ፡፡ ነገር ግን አሁንም የታዘብኩት ነገር ቢኖር በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ አሁንም ፊትአውራሪዎቹ ላለፉት ሰላሳ አመታት ከዚያም በላይ የምናውቃቸው ፊቶች ሆነው ማግኘቴ ነው፡፡ በሰለጠነው አለም የተለመደ እንዲያውም ተቀባይነት ያለው ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ የፕሬዚደንት ኦባማ ጊዜ ምክትል ፕሬዚደንት የነበሩት ጆ ባይደን አሁን ደግሞ ለፕሬዚደንትነት ለመወዳደር እየተዘጋጁ እንደሆነ ሰምተናል፡፡ ይህንን ውሳኔታቸውን ተከትሎ በተለያዩ አካላት አይመጥኑም፣ በተለይ ፆታዊ መስተጋብራቸው ስርዓት ይጎድለዋል ያሉ ከሳሾች ቢነሱባቸውን እሳቸው ግን በሀሳባቸው እንደሚገፉበት አስረግጠዋል፡፡
በእኛ ሀገር ግን  ባለፉት አርባ እስከ ስልሳ አመታት ውስጥ በፖለቲካ ትግል ስም የምነዋቃቸው ግለሰቦች አሁንም የአዲሱ ፖለቲካ ምህዳር ዋነኛ ተዋናይ ሆነው መጥተዋል፡፡ ልምድ እጅግ ትልቅ አበርክቶ እንዳለው የማይስተባበል ቢሆንም ከላይ ያነሳሁት የትውልድና ዘመን ልዩነት እነዚህን ግለሰቦች ውጤታማ ያደርጋቸው ይሆን? የሚልም ስጋት ጭሮብኛል፡፡ ከላይ ወደተነሳሁበት ጉዳይ ልመለስና ንፅፅር ለማድረግ በመሞከር እነዚህ ዘመናትን የተሻገሩ አንጋፋ ፖለቲከኞች በአዲሶቹ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ሊገጥማቸው የሚችለውን ተግዳሮቶች ለማመላከት ልሞክር፡፡
የአመራር ተመክሮ
እነዚህ አዲስ ፓርቲዎችን በነባር መሪዎች ጠርናፊነት ወደ ሜዳው ከገቡ ሊከሰቱ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ከመልካም አጋጣሚዎቻቸው መሳ ለመሳ ለማንሳት ልሞክር፡፡ ተግዳሮታቸው የትየለሌ ናቸው ብለው የሚከራከሩ ብዙዎች አሮጌን ሀሳብ አዲስ ልብ አልብሶ ማምጣት ሲሉት፤ የነባር ፖለቲከኞችን ተሳትፎ የሚደግፉት አካላት ደግሞ "ወይን የሚጥመው ሲቆይ ነው" በማለት ይከራከራሉ፡፡ ለማንኛውም ከሳይንሳዊ መነሻ ጉዳዩን ማየት ለግንዛቤም ለገንቢ ትችትም ስለሚጣቅም ከዚያ እንፃር ለማየት ልሞክር፡፡
በመጀመሪ ደረጃ የትውልድ ልዩነት በሚንፀባረቅበት ተቋም ውስጥ የሚንፀባረቁጽ ችግሮች መነሻቸ የልምድና ተመክሮ ጉዳይ ነው፡፡ ቀዳሚው ትውልድ በአብዛኛው ኑባሬያዊና ተዋረድን የጠበቀ አመራርና አሰራር ለማስፈን እንደሚጥር የእስትራቴጂ ሊቁ ዶ/ር ፒተር ሴነጄ ሲናገሩ፤ የኋለኛው ትውልድ ደግሞ በአመራር ፍልስፍናው ከፈጣንና ልዩነትን የሚፈጥሩ እርምጃዎች ላይ ያተኩራል፡፡ ይህም በዶ/ር ፒተር አገላለፅ  (Traditional/Hierarchical leadership Vs. Dynamic and Breakthrough leadership) ይባላል፡፡
እንደ ዶ/ር ፒተር አገላለፅ በጣም ጥቂት መሪዎች ዘመን ተሻጋር የሚባለውን ሁለቱን እሳቤዎች የማቀናጀትና የመጠቀም አቅም ሲኖራቸው ብዙ መሪዎች ግን ሲቸገሩ ይስተዋላል፡፡ በሆኑም በነባር አመራሮች የሚመሰረቱት አዳዲስ ፓርቲዎች የሁለቱን ዘመን ጠቀስ እሳቤና ልነቶች የማቻቻል አቅምና ችሎታቸው መፈተኛ የቤት ስራዎቻቸው ይሆናሉ፡፡
ሁለተኛው የቀዳሚው ትውልድ በአዲስ ትውልድ ፓርቲዎች ላይ የመሳተፍ ተግዳሮት የእሳቤ አድማስ (imagination) ላይ ያለውን ልዩነት በማንፀባረቅ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የእሳቤ አድማስ (imagination) የነገሮችን ሁለንተናዊ ቁመና (ስፋት፣ ጥልቀት፣ አስቸኳይነት፣ ምስጢራዊነት፣ ጊዜ ተሻጋሪነትና) የመሳሰሉትን ነገሮች ያካተተ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ የእሳቤ አድማስ ልዩነት የጉዳዮችን ትርጉም በግልፅ በትውልዱ መካከል ይፈጥራል፡፡ ይህም ለመግባባትና ልዩነትን ለማቻቻል የሚደረጉ ጥረቶች ጥግ ድረስ የመጓዝ ፈቃደኝነት ኖሮ መልካም መግባባት ቢኖርም፤ ሁለግዜ የሚሳካ ጉዳይ ሊሆን ስለማይችል ልዩነቶች ከባድ ሆነው በሚመጡበት ጊዜ ድርጅታዊ አቋም ሊፈተሽ ይችላል፡፡
ለውጥን በበጎ የመመልከትና የመሻት ጉዳይ (adaptation to change)
ለውጥ የማይቀር ጉዳይ እንደሆነ በርካታ ምሁራን የሚስማሙበት ጉዳየ ሆኖ ሳለ፣ የማትቀረውን ለውጥ መፍራት ወይም ለመከላከል መሞከርን ነባራዊ ተቃርኖ (Existing paradox) ይሉታል፡፡ ምሁራን የመሪዎችን ስራ መፈተሻ መሰንክልም ይኸው ለውጥ እንደማይቀር እየታወቀ የሚፈተር መከላከል ነው፡፡ ምሁራን በለውጥ ጊዜ የሚተሉትን የመከላከል ግባራትን የማክሸፊያ መንገዶች ብለው ካስቀመጧቸው ስልቶች መካከል የለውጥ አካላትንና ተዋንያንን የስሜት ደረጃ በመከታተል ሃለፊነትን መወጣት ሚለው ቀዳሚ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ በመሆኑም ተዋንያንን የመምራት ጉዳይ እጅግ አስፈላጊና አስትራቴጂዊ ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህም ለውጥን በበጎ ለመመልከት የመሻት ሁኔታን ይፈጥራል፡፡
አሮጌ ሀሳብን በአዲስ ልብስ የመምጣቱ ፍርሀት በእኛ
ከግማሽ ደርዘን በላይ ፓርቲዎች ከስመን (እስካሁን ህጋዊ ስርአቱ ተጥሷል የሚለው ጭቅጭቅ ባይቋረጥም) አዲስ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ አቋቁመናል ካሉን ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህም ጊዜ አንደ ሁለጊዘው በርካቶች በተስፋ ትቂቶች ደግሞ በጥርጣሬ ከዚያም ያነሱት ደግሞ በፍርሀት ጊዜ የሚያመጣውን እየጠበቁ ይገኛሉ፡፡ ተስፈኞቹ በአብዛኛው ትንታኔ ሳይኖራቸውና ሳያሻቸው "መልካሙን ነገር የሚያመጣው ፈጣሪ ነው" ብለው የሚያምኑ እንደሆነ ያደረኩት ጥቂት ግምገማ አሳይቶኛል፡፡ ቀሪዎቹ በአዲሱ ፓርቲ መሪዎች ልምድና ተመክሮ ሚተማመኑ ይመስላሉ፡፡  በጥርጣሬ ሁኔታውን የመከታተሉት ደግሞ የሀገራችን ፖለቲካ ከልምድ ከሚገኝ ብስለት ይልቅ ደራሽ ስሜት የሚነዳው ሆኖ ስላገኙት መጠርጠርን መርጠዉ ሚተባበቁ ይመስላሉ፡፡ እነዚህ አካላት ሁኔታዎች ባይሳኩ ማንንም ምክንያት አድርገው ማማረር የሚፈልጉ አይመስሉም፡፡ ይልቁንም በሂደት ሌላ አማራጭና ችግር መፍቻ ዘዴን የሚስቡ ይመስላሉ፡፡ "ፈሪዎቹ" የሰለባዎች ስነልቡና ምርኮኛ የሆኑ ይመስላል፡፡ በእነዚህ ግለሰቦች ላይ ሀሳብ የመስተት ማንም የሞራል የበላይነት ያለው አይመስለኝም፡፡ ይልቁን ጠባሳቸው ለሌሎች ትምህርት ሆኖ እንዲታይ መፈለግ አዝማሚያ ያሳያሉ፡፡
በመጨረሻም የለውጡ ሂዳት በግለሰብ አመራር ላይ ብቻ የሚንጠለጠል እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ነገር የመሪዎች ግንዛቤና አቋም ደግሚ አይነተኛ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም የአዲሱ ፓርቲ መሪ ነባር ታጋዮች ዘመናቸውን መዋጀት ዋነኛ ስራቸው መሆኑ የሰማኛል፡፡ መፅፉም ዘመኑን ዋጁ ይለናልና፣ እዩት መርምሩት አስፈላጊውን ጉዳይ ለዩና ስሩበት ማለት የመስለኛል፡፡
ልቡና ለመሪዎቻችን ዘመናቸውን እንዲዋጁ!!!

No comments:

Post a Comment