Tuesday, 22 July 2025

አሁን አንድ ነገር አሳሰበኝ

 ፕሬዚደንት ትራምፕ ምን እያሉ እንደሆነ አሳሰበኝ!

አቶ ጌታቸው ረዳ በትግል ላይ እያሉ ስለህዳሴ ግድቡ የተናገሩት ነገር ትውስ እያለኝ አሳሰበኝ!

ፕሬዚደንት ትራምፕ ከአንዴም ሶስቴ ለህዳሴ ግድቡ ገንዘብ አሜሪካ ሰጥታለች ሲሉ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ምላሽ ወይም ማስተባበያ ያልተሰጠበት ምክንያት አሳስቦኛል!

ስለዚህ የሚመስለኝን ለመናገር እና ሃሳብ ለማጫር ግድ የሚል ስሜት ስለተሰማኝ የሚከተለውን ሀሳብ አሰፈርኩ፡፡

በቀዳሚ ግን

1.     1. በሁለት ወር ደመወዜን ቦንድ ገዝቻለሁ፡፡ ስለዚህ ግድቡ የግል ጉዳዬ ሆኗል

2.     2. በድርጅት ስም ቦንድ ገዝቻለሁ፡፡ ሰለዚህ በግድቡ ጉዳይ ላይ የሚያገባኝ ሰው ሆኛለሁ

3.     3. በይበልጥ ደግሞ ትምህርት መዝለቄ ለማህበረሰብ የሚገባኝን የጠያቂነት ሚና ለመወጣ እነሆ ጉዳዩን አነሳለሁ፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር ለህዳሴ ግድብ ህብረተሰቡ ያዋጣው 10 በመቶ ያህሉን ነው ብለውናል፡፡ ይህ ማለት 90 በመቶ የግድቡ ወጪ የተሸፈነው በመንግስት የካፒታል በጀን ነው ማለት ይሆናል፡፡ በእርግጥ የመንግስት በጀትም የህዝብ ገንዘብ ነው፤ ነገር ግን በመንግስት አፈጣጠር ፅንሰ ሀሳብ መሰረት መንግስት በግብር እና ታክስ የሚሰበስበውን ገንዘብ በራሱ አሰራር እንዲያስተዳደረው ስለሚፈቅድለት የግለሰቦች ጠያቂነት እምብዛም ጠቃሚ ላይሆን ይችላል፡፡ ግለሰቦች ደመወዜን አውጥቼ ቦንድ ገዝቼ ነበር፤ ቁጠባዬን አውጥቼ ቦንድ ገዝቼ ነበር፤ ስለዚህ የዚህ አስተዋፅኦ ውጤት የታለ ብሎ መጠየቅ ይችላል፡፡

በእርግጥ የመንግስት በጀትም በእቅድ ተዘጋጅቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የሚወሰን እና አፈጻጸሙም በዚያው ቁጥጥር የሚደረግበት ስለሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ዜጋው ይቆጣጠረዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ይታሰባል ያልኩት አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ይህንን ያሳያል ብዬ ስለማላምን ነው፡፡

ይህንን ለጊዜው ልተወውና የህዳሴ ግድቡ የገንዘብ ምንጭ ጉዳይ ታዲያ ምን ይመስላል ወደሚለው ወደ ወሳኙ ጥያቄ ላምራ፡፡

እኔ ፕሬዚደንት ትራምፕ የተናገሩትን ለማመን እየዳዳኝ ነው፡፡ ምክንያቶቼ የሚከተሉት ናቸው፡፡

1.     1. ፕሬዚደንቱ ከአንዴም ሶስቴ ጉደዩን ሲያነሱ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ምንም መልስ ያልተሰጠበት ምክንያት እንድ ነገር ቢኖር ነው አሰኝቶኛል፡፡

2.     2. መንግስት ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ላይ እንደነበር፤ አሁንም እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ በተለይ የሰሜኑ ጦርነት እንዲሁም በአለም አቀፍ ደረጃ ያሉ አለመረጋጋቶች በአለም የእቃዎችን ዋጋ በማናር ተግዳሮት እንደፈጠሩ እረዳለሁ፡፡ በመሆኑም መንግስት ገንዘብ ለማግኘት ይፋ ያልወጣ ውል ከመንግስታት/ከሌሎች አካላት ጋር ተዋውሎ ሊሆን ይችላል፡፡ የግልፀኝነታ ችግር ባለበት የሀገራችን ፖለቲካ ይህ ቢሆን አይገርመኝም

3.     3. አቶ ጌታቸው ረዳ በተደጋጋሚ “ግድቡ ተሸጧል” ብለው ሲናገሩ እንደ ማንኛውም አሉባልታ ላየው አልችልም፡፡ ስለዚህ ግለሰቡ እስካላስተባበሉ ድረስ በግድቡ ስም የተገኘ ገንዘብ አለ ብዬ እንዳስብ አስገድዶኛል፡፡

በመሆኑም የህዳሴው ግድብ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤቱም ይሁን መንግስት መረጃ የመስጠት ሀላፊነታቸውን በመወጣት ጉዳዩ እንዲጠራ እንዲያደርጉእንደዜጋ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡