Tuesday, 5 June 2018

የጋዜጠኛና ጋዜጠኝነት ተግዳሮቶች በአሁኑ ዘመን


የጋዜጠኛና ጋዜጠኝነት ተግዳሮቶች በአሁኑ ዘመን
ጌታቸው መላኩ
ግንቦት 23 2010
አዲስ አበባ

በዘመናችን ሰዎች ለቁጥር በሚያዳግቱ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ አነዚህም ለሰዎች የቀን ተቀን ኑሮ ገቢ ከሚያስገኙት እስካ ሙያዊና ህይወታዊ ጥሪ ሆነው የሚከወኑትን ስራዎች ያካትታል፡፡ ነገር ግን  በሁሉም ዘርፍ ውጤታማነት ተዋናዩን ሁሉ የሚያስደስት ነው፡፡

አንዳንድ ስራዎችን ጊዜና ሁኔታዎች ይገድቧቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ አላማቸውን በብቃት ሲያሳኩ አይታዩም፡፡ ለምሳሌ የማምረቻ ፋብሪካዎች የስራ ሰዓት አዋጅ፣ የሀይል አቅርቦት የድርጅቶቹ የስራ ሰዓት ስምሪት አቅምና ሌሎችም ነገሮች የገድቧቸዋል፡፡ ለእነዚህ ገዳቢ ኩነቶች ምላሽ በመስጠት የ24 ሰዓት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ጠቋማት እንዳሉ ያጤኗል፡፡
የሁሉም ተቋመት ግብ ቢያንስ በአላማ ደረጃ ግን አቅማቸውን አሟጣ በመጠቀም ውጤታማና ትርፋማ መሆን እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡
ተቋማት የሰዎች አስተሳሰብ መገለጫና ውጤት ናቸው፡፡ ከላይ የገለፅናቸው በተላያዩ ሁኔታዎች የተገደቡም ይሁኑ ለእነዚህ ሁኔታዎች ምላሽ ሰጥተው ሙሉ አቅማቸውን ለመጠቀም የሚታትሩ ተቋማት የመሪዎቻቸውና የሰራተኞቻቸው የአስተሳሰብ አይነትና ደረጃ መገለጫዎች ናቸው፡፡ በማናቸውም ሁኔታ ግን ስራን በውጤት መተርጎም በአስተሳሰብ ደረጃ የማንኛውም ተቋም ባልደረባ አላማና ፍለጎት ቢሆንም፤ ተግባራዊ መገለጫው ግን ግንዛቤ ደረጃውና በልምዱ ከሰዎች ሰዎች ይለያያል  አንዳንዴም ጭራሽ አይገጥምም፡፡
ባለንበት ዘመን ሰዎች ወደስራቸው ሲገቡ ባለፈው የስራ ቀን የጀመሩትን ዛሬ ለመቀጠልና የስራ ሰዓት እስኪገባደድ ጠብቀው ለመተግባር ከሆነ ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ ይመስለኛል፡፡ ማንኛውም ስራ የሚፈልገው የእውቀት የክህሎትና የአመለካካት ደራጃ የሚለያይ የማቀድና ውጤትን የማለም ተዘክሮ አለው፡፡ የውጤት ተኮር ስራ አመራር "በአጋጣሚ" ከቀየራቸው የጥበቃ ሰራተኞች ልምድ እንደተረዳሁት እምነታቸው የሚጠብቁት ንብረት በተሰማሩበት ቀንና ሰዓት አለመጉደሉን ማረጋገጥ ዋና ተግባራቸው ቢሆንም ንብረቱ ለስርቆት ሊዳረግ የሚችልበትን መንገድና አጋጣሚ ቀድሞ በመለየት አደጋን ቀድሞ ማስወገዱ ከተራ ሰራተኝነት የዘለለ ባለሙያ እንደሚያደርጋቸው አምነው ተቀይረዋል፡፡ በመሆኑም ስራ ከተራ የዕለት ከዕለት ተግባር ባለፈ ሙያዊ ተሰጥቶና አስተዋይነት ወደሚለካበት የአተገባበር ደረጃ  ካላደገ አሰልቺ፣ ውጤት አልባና በስተመጨረሻም ተጠያቂነትና ጉዳት ላይ የሚጥል ውጤት እንደሚመጣ እሙን ነው፡፡
እንዳንድ ስራ ዘርፎች ከሌሎች በተለየ እቅድ ሲሹ አንዳንዶች ደግሞ ልዩና ተገማች ባለሆኑ አጋጣሚዎችና ሁነቶች የተከበቡ በመሆኑ ለተግባራዊነታቸውና ውጤታቸው የተለየ ትኩረት ይሻሉ፡፡ ይህም የሚረጋገጠው በእቅድ ጊዜ በሚደረጉ ጥልቅ ግምገማዎች ነው፡፡
በታሪክና ባህል ከአለም ዋነኛዋ ሀገር የነበረችው ሀገራችን በዕድገትና በስልጣኔ ግን እስካሁን በዝግመት ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህም ዘመን የሶስተኛ ዓለም ሀገር ተብለን የምነጠራ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ (1990ዎቹ እ.አ.አ) አዳጊ ሀገር የሚል የማፅናኛ አይነት ስም ተለጥፎልናል፡፡
ይህ የሆነበት ምክንያት ለግምት የሚያዳግት ቢሆንም፤ ብዙዎች መረጃ እያጣቀሱና እየተነተኑ የየራቸውን ሀሳብ ያቀረቡበት ጉዳይ ስለሆነ ወደዚ መግባቱ ለጊዜው አስፈላጊ አይደለም፡፡ አንዱና ዋነኛው ችግር ግን ባለሙያነት የመጥፋቱና ስሜቱም  የመድከሙ ጉዳይ ሲሆን በዚህ ፅሁፍ ለማየት የተመረጠውም ይኸው ጉዳይ ነው፡፡ በዘመናችን ካለመው የጋዜጠኝነት ስራ ክዋኔ አንፃር እንደሚከተለው ታይቷል፡፡
ባለሙያ ማለት በቀላሉ ሙያን ገንዘቡ ያደረገ ማለት ነው፡፡ ሙያን ነጥለን ወስደን ስናይ ደግሞ ተግባርን በመለየት በመተንተን አቅዶ በተለያዩ መለኪዎች ውጤታማ የመሆን ስራን ያመለክታል፡፡ የስራ ዘርፍ ተመራማሪዎች የሙያተኛን ውጤታማነት በሶስት መለኪያዎች ይለኩታል፡፡ እነዚህም ጥራት፣ ብዛትና ጊዜ ናቸው፡፡ በመሆኑም የዘመናችን የጋዜጠኝነት ተግባር እንደ ስራ ሲታይ ጋዜጠኛው እንደባለሙያ ሲለካ ምን ይመስላል? በተለይተግዳሮቱስ ምንድን ነው?
በዘመናችን ያለ ጋዜጠኝነት ተግዳሮቶች መገለጫ ከሆኑት ተግባራት መካከል በዕለት ደራሽ ስራ መጠመድ፣ መረጃ ማግኘትን የስራው መጀመሪያና መጨረሻ አድርጎ መውሰድ፣ በጊዜ ሂደትና በጠንካራ ስነምግባር በሙያው የሚያድግ ባለሙያ እንደሚኖር መዘንጋትና ከግል አቅምና አቋም የዘለለ እይታ መገደብ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ከዚህ በመቀጠል እነዚህ አስተሳሰቦች እንዴት በሀገራችን የጋዜጠኝነት መህዳር ውስጥ ተግባራዊነታቸው እየሰፋ እንደመጣና ውጤታማነትን እየፈተኑ እንደሆነ እንመልከት፡፡
በእለት ደራሽ ስራ መጠመድ
ጋዜጠኛው የመስሪያ ቤት አደረጃጀት ሰለባ የሆነበት የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሀን ዘርፍ ዜናም ይሁን ዝግጅት በስምሪት የተባለ በሚመስል ተግባር እንደተጠመዱ ያመላክታል፡፡ በመሆኑም እቅድ ለይስሙላና ለስብሰበ ማጣፈጫ ከመወራቱ የዘለለ በመገናኛ ብዙሃን ተግባር የሰማይ ያህል የራቀ እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡
አሳሳቢው ጉዳይ ይህ ባህል ሆኖ በጀማሪ ባለሞያዎች ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተፅዕኖ ነው፡፡ ባለሞያዎች የጋዜጠኝነት ሞያ የዕለት ደራሽ ስራ የወጠረው ተግባር ሆኖ የዕቅድና የክትትል ዜናና ዘገባዎች ከጋዜጠኝነት ድርሳን እንዳይፋቁ የሚሰጋበት ዘመን ላይ እንደሆንን ብዙዎች ይነሳሉ፡፡
በድንገት ደራሽ ስራ መጠመድ የስራ መጀመሪያና መጨረሻ የሆነላቸው ጋዜጠኞች የዚህን ትግበራ ትሩፋቶች ከገፀ በረከትና ንዋይ ጥቅም አንስቶ ብዙ አውሪ ትንሽ ስሪ እንዳደረጋቸው ለማወቅ ከላይ የተጠቀሱትን መለኪያዎች በጥቂት ሞያተኞች ላይ በመተግበር ማየት ይቻላል፡፡
የስራን ክብደትና ቅለት የመለኪየው የሚያመጣው ውጤትና የሚፈጥረው ተፅዕኖ መሆኑ ቀርቶ ጋዜጠኛው ለጉዳዩ ጥንቅር የወሰደበት ጊዜና የጉልበት (በእንቅስቃሴና በማሰብ) መሆን መጀመሩ ከቀን ተቀን እንቅስቃያችን ማየት ጀምረናል፡፡
የእለት ደራሽ ስራ የፈጠራቸው ዕለት ደራሽ ጋዜጠኞች ተስፋና እርግማን በራሳቸውና በአስተማሪ አለቆቻቸው እጅ ነው፡፡ ቀደሞ የነቃና ተስፋውን የመረጠ ባለሙያ ቢኖር መጀመሪያ ማድረግ ያለበት ከዚህ አሰራር የሚወጣበትን ዕቅድ ለራሱና ለባልደረባው መስራት ነው፡፡
መረጃ ማግኘትን የሰራው መጀመሪያና መጨረሻ አድርጎ መውሰድ
በዘመናችን የማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ይህንን ጉዳይ ፉርሽ ያደረጉት ቢመስልም ጋዜጠኛው አሁንም የዚህ ተግባር / አስተሳሰብ ተጎጂ ነው፡፡ብዙዎች ራሳቸውን ለመከላከል የማህበራዊ መገናኛ ብዙኃንን ተአማኒነትን እያብጠለጠሉ  መረጃቸው ያልተጣራና ሙያዊ ስነምግባር የጎደለው ነው እያሉ ቢያነሱም፤ ከእነሱ የበለጡ ብዙዎች ደግሞ ጭራሽ እነዚህኑ የመረጃቸው ምንጭ ሲያደርጓቸው ይስተዋላሉ፡፡
የዘመናችን ጋዜጠኝነት ሰበር ዜና ማቅረብ የቀደመ ምን ብላ ….. አይነት ጨዋታ አድርጎታል ፡፡ የዚህ ጨዋታ ተጎጂ ደግሞ ጋዜጠኛው ራሱ ነው፡፡
በእውነት መረጃ ማግኘት ብቻ የጋዜጠኝነት ስራ መጀመሪያውና መጨረሻው ይሆን?  አንድ የእንግሊዝናኛ አባባል አዘውትሬ በትምህርትና ስራ ላይ እጠቀማለሁ “የተፃፈ ሁሉ ሊጠየቅ እንጂ እንዲሁ ሊቀበሉት አይገባም” መረጃ ያገኘ ጋዜጠኛ ሁሉ ባለሙያ የሆነ እየመሰለው ለሞያውና ለራሱ ሃፍረት እየሸመተ ያለባቸው ተግባራት ከግዜ ወደ ግዜ እየተበራከቱ መጥተዋል ፡፡
ድህረ ገፅ ላይ ዜና ወይም ሃተታ ለጥፎ መልሶ ማንሳት፤ ያልተሟላ መረጃ አትሞ ማስተባበያ ለማውጣት መራወጥ፤ የማይወክል ጉዳይ አስተላልፎ የይቅርታ መግለጫ ለማንጋጋት መጣር የዘመናችን ጋዜጠኞች መገለጫ ከሆኑ ውለው አድረዋል፡፡
አንድ ጋዜጠኛ መረጃ ማግኘቱ መጀመሪያው ቢሆንም መረጃው ለታዳሚ የሚኖረውን ፋይዳ መመርመር ከቻለ ዕሴት ጨመረበት ፤ ከዚያም አልፎ አቀራረቡን አወቀበት ፡፡ ይህም ባለሞያ የሚያሰኘው ተግባር ይሆናል ፡፡ በቅርቡ በአንድ መገናኛ ብዙኃን የአንድ አካባቢ የአየር ሁኔታ ዘገባ ሲሰራ የቦታው ከፍተኛ የሙቀት መጠን 80 ዲግሪ ሴልሽየስ ነው ብሎ ያቀረበ ጋዜጠኛ አስታውሳለው፡፡
ይህ መሰረታዊ እውቀትን የሚፈትን ዘገባ የጋዜጠኛው የ"መረጃ መጀመሪያና መጨረሻ" ጉዳዩ የሰረፀበትን ደረጃ አመላካች ሲሆን አንድምታው ግልፅ ነው፡፡ መረጃ ለማግኘት መፈልፈል መበርበር የጋዜጠኛ ስራ ነው ፡፡ መመርመር መተንተንና ማበጠር ይከተላል ፡፡ በመጨረሻ ለታዳሚ እንደሚጠቅም ማቅረብ ይሰልሳል፡፡
ይህ የመሰረታዊ የጋዜጠኝነት ተግባር ሀሁ መሆን ሲገባው በዕቅድ እንኳ ሊሰራ ያልቻለ ከፍተኛ ደረጃ ተግዳሮት ሆኖ በኢትዮጵያ ብዙኃን መገናኛ ድባብ ላይ ይታያል፡፡
በጊዜ ሂደትና ጠንካራ ስነምግባር በሙያው ያለማደግ
የመገናኛ ብዙኃን ከሌሎች የሙያ ዘርፎች የተቀዱ የስራ መደቦችና እርከኖች ሲጠቀሙ ይስተዋላል፡፡ ከጀማሪ ዘጋቢ እስከ ዋና አዘጋጅ ያሉ ስያሜዎችም የብዙዎች የደብዳቤ ሲያልፍም የመታወቂያ ወረቀት መገለጫዎች ሆነዋል፡፡ ይህ በራሱ ችግር ባይኖረውም በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ግን ሁሉም ተቀላቅሎ አንድ ሆኗል ፡፡ ይህንንም ያመጣው  “ጋዜጠኛ” የሚለው የውል ስም ይመስለኛል፡፡
የጋዜጠኝነትና የተግባቦት ትምህርት ቤት በኢትዮጵያ ከአጫጭር ስልጠናዎች ደረጃ ተነስቶ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ የሚሰራበት የትምህርት ዘርፍ ሆኗል የቀደሙት የመገናኛ ብዙኃን ማሰልጠኛ ተቋማትና ማሳያዎች ናቸው፡፡ዋናው ጉዳይ እነዚህ ተቋማት ባለሞያ ፈጥረዋልን? የሚለው ነው፡፡ ከሌሎች ሞያዎች ጋር ማነፃፀር የዚህ ፅሁፍ አላማ ስላልሆነ ወደዛ አልገባም፡፡
ነገር ግን ጋዜጠኝነት በግዜ ሂደትና በጠንካራ ስነምግባር በሙያ ልህቀት የሚታይበት ዘርፍ መሆኑ አጠራጣሪ እንደሆነባቸው ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ሙያ ከሚከፈል ተራ የስምሪት ይበልጣል ፡፡ ሞያ ወጣኒነት(ጀማሪነት) አዳጊነትና ብቁነት የሚታይበት የስብዕናና የአመለካከት መገለጫ ነው፡፡
ሙያ በዕቅድ ተሰርቶ የሚለወጡበትና የሚበቁበት ልዩ ፀጋ ነው፡፡ ሙያ መጨረሻ ለሌለው የእውቀት አለም ዜግነት ማግኛ መለያ ነው፡፡ በአገራችን ጋዜጠኝነት በአንድ ጀንበር ተንታኝ የሚኮንበት በሚቀጥለው ቀን መፍትሔ አመላካች ሊቅ የሚኮነንበት በሶስተኛ ቀን ያላየነው የለም የሚባልበት አሳዛኝ ዘርፍ ሆኗል ብለው ብዙዎች ያማርራሉ፡፡
ጋዜጠኝነት በታቀደና በተመረመረ ስራ የሚያድጉበትና በስብዕና የሚበለፅጉበት አልፈውም ለታዳሚ እሴት የሚሆኑበት ምዕራፍ ሊዘጋ አንድ እሁድ ቀረው ብለው ያዝናሉ ይቆጫሉ፡፡ በመሆኑም ጋዜጠኝነት በግዜ ሂደትና በጠንካራ ሞያዊ ስነምግባር ለማደግ የማይተጋበት ዘርፍ ለምን ሆነ ብለው ቢጠይቁ መልሱ ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለውም ይመስለኛል፡፡
በዕቅድ መመራትና በውጤት መለካት ከጋዜጠኝነት መንደር ኮብልለዋል፡፡ ይኽውም ለአቋራጭ መንገድ ተጠቃሚዎች በሩን በሰፊው ከፍቷል፡፡ ብዙዎች የባለስልጣናት ረዣዥም እጆችና የፖለቲካ ስርዓት ተፅዕኖዎችን በመጥቀስ ችግሩን በሌሎች ሊያላኩ ቢሞክሩም በራሳቸው መከራከሪያ ነጥብ ራሳቸውን ይጠልፋሉ፡፡ ባለቤቱ ያቀለለውን እንዳልን ከላይ!!
ከግል አቅምና አቋም ያልዘለለ ዕይታ
ዘመኑ ለጋዜጠኞች ዶሮ ብታልም ጥሬዋን ነው የሆነባቸው ይመስለኛል፡፡ ዕውቀትን በራሳቸው ትንሽ ቁና የሚሰፍሩ፣ መረጃን በራሳቸው የዕይታ አድማስ ውስጥ የሚፈልጉና፣ ጥበብን በራሳቸው የዕውቀት አድማስ ልክ ብቻ የሚተነትኑ ጋዜጠኞች በዝተዋል ብቻ አይገልፀውም፡፡ በእርግጥ አንድ እውነታ አለ አንድ ስራ መጀመሪያ ሰሪውን ካላረካ ሌላውን ያረካል ለማለት ይከብዳል፡፡
ነገር ግን ሰሪውና ስራው ማንና ምን ናቸው? የሚለውን እዚህ ጋር ማጤን ያስፈልጋል፡፡ በአንድ አጋጣሚ አንድ ጋዜጠኛ ጣቢያው የሰራው ልዩ ፕሮግራም ከሌላው የተሻለ እንደሆነ ሲገልፅልኝ የተየኩት አንድ ጥያቄ ብቻ ነበር እርሱም “በማን መለኪያ” የሚል ነበር በሰሩት ስራ መርካት ችግር የለበትም ችግሩ የሚጀምረው የሰሩት ስራ ለሌሎች ስራዎች ማንፀሪያነት የደረሰ የመጨረሻ ተግባር ነው ብለው የወሰዱት ግዜ ነው፡፡ በመሆኑም ጋዜጠኞችና መገናኛ ብዙኃን በራሳቸው አቅም ልክ ታዳሚን መገመት ሲጀምሩ የመጨረሻው መጀመሪያ ይሆናል፡፡
የዘመናችን ጋዜጠኞች ሌላው ችግር የግል አቋምን የአብዛኛው አቋም አድርጎ መሳል ነው፡፡ ይህ ነገር ካለማስተዋል ከሆነ በምክርና በትችት ሊስተካከል ይችላል ነገር ግን ሆን ተብሎ የተሰራ ከሆነ መመለሻው አደገኛ ማጣፊያው አጭር ይሆናል፡፡ የዚህ ፅሁፍ አንባቢም ይህ ትንተና በአቅምና በአቋም ላይ ተመስርቶ በበጎ ለበጎ የተዘጋጀ እንደሆነ ይረዳው ዘንድ እለምናለው፡፡
የጋዜጠኞች ከግል አቅምና አቋም ያልዘለለ ዕይታ የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ ከላይ እንደተገለፀው አንዱና ዋነኛው መረጃ ማግኘትን የመጀመሪያና የመጨረሻው አድርጎ መውሰድ ነው፡፡ በመሆኑም መረጃን ለመጠየቅና ልምድ ያለመኖር የአቅም ውስንነትን ያመጣል፡፡
ሌላው ምክንያት በግዜ ሂደትና በጠንካራ ስነምግባር በሙያው ያለማደግ ነው፡፡ በመሆኑም ጋዜጠኞች ጉዳዮችና የመመርመርና የመተንተን ችሎታና ፍላጎት ሲከዳቸው አቋም አራማጆች ሆነው ያርፉታል፡፡  ዘወትር እንደሚነሳው ሁነኛ የቃለመጠይቅ ጥያቄ ማዘጋጀት እየተሳናቸው ጥያቄዎቻቸው "ምን ይላሉ?" እና "ምን ይሰማዎታል?" የሚል ይሆናል፡፡
አንዱ ጋዜጠኛ አንድ እንግዳውን ምን ይሰማዎታል ብሎ ቢጠይቅ ችብግዳው "ንዴት" ብሎ መለሰለት መልሱ ያልተዛመደለት ጋዜጠኛ "በምን?" ቢለው "በአንተ ተራ ጥያቄ" ብሎት ሄደ የሚል ቀልድ ብዙዎቻችን የሰማን ይመስለኛል፡፡
ምን ይሻላል?
ጋዜጠኝነት በእለት ደራሽ ስራ ብቻ የመጠመድ አባዜ አይደለም፡፡ ነገር ግን ጋዜጠኝነት በጊዜ ሂደትና በጠንካራ ስነ ምግባር በሙያ የሚያድጉበት፣ መረጃ ማግኘት የስራው መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ ያልሆነበት፤ ይልቁንም ከግል አቅምና አቋም የዘለለ ሰፊ ሞያዊ ዕይታን የሚፈልግ መመርመርን የሚሻና አዘውትሮ መጠየቅን የሚያስገድድ ተግባር ነው፡፡
በመሆኑም ይህ ጉዳይ የማይሆንበት ሁሉ አቋርጦ ቢመለስ፤ ለመቆየት የወሰነ ካለ ግን የስራውን ባህርይ ተገንዝቦ ራሱን ማትጋት ይገባዋል፡፡ የስራ መሪዎች ፤ የትምህርትና የስልጠና ተቋማት በዘርፉ የቆዩ ባለመያዎች ራሳቸውን የሚፈትኑበት ጊዜ ቢያልፍም "ከመቅረት መዘግየት ይሻላል" እንዲሉ በቀረው ጊዜ ሁኔታዎችን ለማስተካከል ቢሰራ መልካም ነው፡፡
ምን ይሰራ?          
"እዳው ገብስ ነው" ይባላል ችግሩ በሌሎቹ ዘርፎችም እንዳለ ሁሉ የሙያውን አላማ ጠንቅቆ ማወቅ የብዙሃን መገናኛዎች ራዕይና አላማ አበጥሮ መለየትና ከሚሰሩት ስራ ሁሉ ውጤቶችን መጠበቅ ናቸው፡፡ አንደኛ ራስን መለወጥ ሁለተኛ ሌላውን /ታዳሚን ለመለወጥ ማቀድ፡፡
ይህስ ከሆነ በኋላ ሁሉም ነገር መልካም ይሆናል ማለት ነው? ውጤታማነት ይጎላል ማለት ነው? መልሱ "ይሆን ይሆናል" ይመስለኛል ፡፡ በእርግጠኝነት የሚታወቀው ደርሰን ስናየው ብቻ ነው፡፡ ሌሎች ሄደዋላ!!